አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

አንጋፋውና ፋና ወጊው የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ኮሌጅ የተመሠረተበትን 80ኛ አመት ማክበር ጀመረ።

ነሀሴ 28 ቀን 2014 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ የተመሠረተበትን 80ኛ አመት ክብረ- በዓልን ከዛሬ ጀምሮ በተለያዩ ሁነቶች ማክበር ጀምሯል።

በዛሬው የመክፈቻ መርሀ-ግብር የተገኙት የስራና ክህሎት ሚንስቴር ሚንስትር ክብርት ሙፈሪሀት ካሚል ባደረጉት ንግግር እንኳን ለ80ኛ አመት የምስረታ በዓል አደረሳቹህ በማለት ኮሌጁ አንጋፋ እንደመሆኑ መጠን ለሌሎች አርአያ በመሆን የሚያሰለጥናቸው ሰልጣኞች ስልጠናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ስራ የሚፈልጉ ሳይሆኑ፣ በኮሌጅ ቆይታቸው ስራ ፈጥረው የሚወጡ እንዲሆኑ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ቴክኒክ፣ ሙያና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ ወ/ት ፀዳለ ተክሉ የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ኮሌጅ በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ታሪክ የመጀመሪያው መሆኑን ገልፀው፤ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት ምክንያት ኮሌጁ የተፈጠረለትን አቅም እንዲሁም ለ80 አመታት ያካበተውን ልምድ እና የገነባውን መልካም ስም እንደ እድል ተጠቅሞ የስራ ገበያ ፍላጎትን መሠረት በማድረግ የሚሰጣቸውን አጫጭር እና መደበኛ ስልጠናዎችን በበለጠ ጥራት በመስጠት በቴክኒካል ክህሎት የበቁ እና ጠንካራ የስራ ባህልን የተላበሱ ዜጎችን በብዛት ማፍራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

ሌላው በምስረታ በአሉ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ  የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ የስልጠና ስራውን አንድ ብሎ ከጀመረበት ከ1934 ዓ.ም ላለፉት 80 አመታት አገራቸውን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያገለገሉ እና በማገልገል ላይ የሚገኙ በርካታ ስመጥር ባለሙያዎችን በማፍራት በአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ የመጣ መሆኑን ገልፀው ኮሌጁ የትላንት ጥንካሬውን ይዞ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል።

የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የኮሌጁ ዋና ዲን አቶ ግሩም “የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የዛሬ 80 አመት በ1934 ዓ.ም ሲመሠረት በጣም በጥቂት የውጪ አገር ባለሙያዎች እና በአነስተኛ ግብአት መሆኑን ገልፀው፣ ዛሬ ላይ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ተጠቃሚ በመሆኑ ከ60 በላይ ወርክ ሾፖች ከተሟላ ማሽንና የእጅ መሳሪያዎች እንዲሁም የበርካታ የአስተዳደር እና ንድፈ-ሀሳብ ማስተማሪያ ህንፃዎችን በመያዝ በየአመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 5 አሰልጥኖ በማስመረቅ ላይ ይገኛል ብለዋል።

ኮሌጁ 80ኛ አመት የምስረታ በአሉን ምክንያት በማድረግ ግንባታቸው የተጠናቀቁ ሁለት ባለ G-7 ህንፃዎችን እና የ80ኛ አመት ሎጎ አስመርቋል፡